ታሪክ

ደብረ ጽዮን መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፤ ቺካጎ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመካከለኛው የአሜሪካ ግዛት ለመጀመሪያ ጊዜ መሠረቷን የጣለቺው በቺካጎ ከተማ ሲሆን ዘመኑም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1975 ዓ/ም ነበረ። አገልግሎቱንም የጀመሩት እና በአካባቢው የመጀመሪያውን ቤተ ክርስቲያን ያቋቋሙት ክቡር ሊቀ ሊቃውንት አባ ተክለ ሚካኤል (ነሲቡ) ታፈሰ ናቸው። በጊዜው አብዮቱን ተከትሎ በሀገራችን በኢትዮጵያ ከነበረው ችግር የተነሣ ክቡርነታቸው ወደ ቺካጎ ተሰደው ከመጡ በኋላ የነገረ መለኮት ድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን በተከታታይ ሁለት በማስተርስ እንዲሁም አንድ አንድ በፒኤችዲ ደረጃ ከተለያዩ ሦስት ትምህርት ቤቶች ዘንድ በመከታተል ላይ በነበሩባቸው ዓመታት በአካባቢው የነበሩ ኢትዮጵያውያንን እያሰባሰቡ የማኅበር ጸሎት ያደርጉ ነበር።

አባታችን ጥቂት ኢትዮጵያውያንን ማግኘታቸው ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ሰብሰብ ብለው የሃይማኖትና ያገልግሎት ተቋም ለመመሥረት ያላቸውን ፍላጎት አጠናክሮት ነበር። ምንም እንኳን የሚከታተሉት ትምህርት ፋታ የማይሰጥ ቢሆንም በተጓዳኝ የቤተ ክርስቲያኑን አገልግሎት አጣምሮ ለማካሄድ እንደሚቻልም አምነዋል። በዚያን ጊዜ ነበር ከግብጻውያን ኦርቶዶክስ ወንድሞቻቸው ጋር ቀድሞም የነበራቸውን አሁንም የቀጠሉትን ግንኙነት አጠናክረው ከቺካጎ በስተምዕራብ ሮዜል ከምትባል ከተማ ከግብጻውያኑ የቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ካሕናት ቤተክርስቲያናቸውን ለተወሰኑ አገልግሎቶች ያስፈቀዱት።

Picture Aba

የመጀመሪያው ሥርዓተ ተክሊል በቺካጎ

ይህ በዚህ እንዳለ አንድ ቀን ከኖርዝዌስተርን ዩኒቨርሲቲ መምሕራን ጋር በሚጨዋወቱበት ወቅት የዶ/ር ታደሰ ታምራትን ከዚያ መኖር ይሰማሉ(ዶ/ር ታደሰ በሥጋ ሞት ተለይተውናል)። መምህራኑም ዶ/ር ታደሰን በቅርብ ያውቋቸው ስለነበር መምሕራኑ በስልክ እንዲገናኙ አድርገው በናፍቆት ሊገናኙ ቻሉ። ውሎ ካደረ በኋላ ዶ/ር ታደሰን የሚያውቁ ሁለት እጮኛሞች ጋብቻቸውን ለመፈጸም ይጓጉ የነበረው ቢቻል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት መሆኑን ያጫውቷቸዋል።

ዶ/ር ታደሰም እስቲ ቆዩ! እኔ በቅርብ የማውቃቸው አባት፣ አባ ተክለሚካኤል የተባሉ ከዚህ አሉ ፣ ምናልባት ሊፈጽሙላችሁ ይችሉ ይሆናልና እስቲ ላማክራቸው በማለት ለአባታችን ያማክሩአቸዋል።

አባታችንም በደስታ እንደሚያደርጉትና የተፈቀደላቸውን የቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ አስረድተው አንድ ያላቸውን ችግር፣ ረዳት ዲያቆን አለመኖር ለዶ/ር ታደሰ ይገልጹላቸዋል። ዶር/ ታደሰም ኮራ ብለው እንዴ አባ ! እኔ እኮ የተካንኩ ዲያቆን ነኝ ፤ ዘነጉት እንዴ ! በማለት ረዳት ሊሆኑ መቻላቸውን አረጋግጠውላቸው በቺካጎ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥነ ሥርአት በኢትዮጵያዊ ካሕን በቺካጎ የነበሩ ጥቂት ወዳጅና ዘመዶች አጅበዋቸው የመጀመሪያው ጋብቻ ለወ/ት ዘውዲቱና ለአቶ ሙሉነህ አዘነ በተክሊል የተፈጸመላቸው መሆኑን ቤተክርስቲያናችን መዝግባለች።

የመጀመሪያው የክርስትና ጥምቀት በቺካጎ

ይህ የተቀነባበረ አሠራርና አገልግሎት ለተከታታይ እርምጃ ከፈት ያለ በርና የተጠናከረ ተስፋ እያስገኘ ሄደ። የኢትዮጵያውያኑም ቁጥር ተበራከተ። አቶ ጃርሶና ወይዘሮ የሻሽ ወርቅ ደምበል ጥቂት ቀደም ብለን በመጀመሪያ ልጃቸው መወለድ ያወቅናቸው በኋላም በሃይማኖት ጥንካሬ መደርጀት ይመሩ ከነበሩት ውስጥ የነበሩ የልጃቸው ክርስትና መነሻ ጊዜው እየተቃረበ ሲመጣ አባታቻን አገልግሎቱን እንዲፈጽሙላቸው መጠየቁ አዋኪ አልነበረም። እንደመጀመሪያውም ጋብቻ የክርስትና ጥምቀቱም ተቀነባብሮ በቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን በሮዜል ከተማ በቺካጎ የመጀመሪያው የክርስትና ጥምቀት በአባታችን በአባ ተክለሚካኤል ለእሌኒ ጃርሶ ተፈጽሞላታል፤ ስመ ጥምቀቷም አስካለማርያም ተብሎ ተሰይሞአል። አስካለማርያም የመጀመሪያዋ የቤተክርስቲያናችን ክርስትና ጥምቀት ተቀባይ ስትሆን ለብዙ ዘመናት የቤተክርስቲያናችን አገልግሎት አካል የነበሩት ወ/ሮ ገነት ብፅአትና አቶ ሞላ ወልደሥላሴ የመጀመሪያ የክርስትና እናትና አባት እንደሆኑም ይታወሳል።

የመጀመሪያው ማኅበራዊ ስብሰባ

እነዚህ የሃይማኖታችን መሠረታዊ አገልግሎቶች በተለይ የክርስትና ጥምቀት እየጨመረ መሄድ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮችን ቶሎ ቶሎ ሊያገናኝ ቻለ። በዚህ እድል ለመጠቀምና ጽኑ እምነት ላይ የተመሠረተ ማሕበር ለማቋቋም ተገቢ መሆኑን አባታችን ከጥቂቶች በሃሳቡ ተባባሪዎች ጋር ከተወያዩ በኋላ በርከት ያሉ ሰዎችን የሚያቅፍ ስብሰባ እንዲደረግ ተወሰነና አባታችን ከሚኖሩበት 4750 ሰሜን ሸሪዳን ሕንጻ ውስጥ እንድንሰባሰብ ተቆርጦ በመጀመሪያ ስብሰባችን በቁጥር ከሃያ የማንበልጥ ልንገናኝ በቃን። ይህ የመጀመሪያው የተቀናበረ ስብሰባ ነበር። አባታችን ስብሰባውን ከባረኩ በኋላ እራሳቸው ወዳዘጋጁልን ቁርስ መሩንና እንድንሳተፍ ጋበዙን። የሚያስጎመጅ በአዋዜ ቅብ የተዋበ የዳቦ ድርድር ነበር። እያነሳን እያጣጣምን መብላት ጀመርን። አባታችን እንዲህ ያለ ስብሰባ ደገም ደገም ቢያደርጉ አይከፋም ያሉ በርካቶች ነበሩ። ወንዶቹ ወደመቀመጫችን ስናመራ ሴቶቹ አባን ከበብ ከበብ አድርገው ጊዜ ወሰዱ፤ ምነው ምንድነው ነገሩ ቢባል የአዋዜውን አዘገጃጀት (ሬሲፒ) ለማወቅ እየሞከሩ መሆኑን ተረድተን ይገባል እያልን ስብሰባውን ጀመርን። ከዚያም ስብሰባው በሚያስደስት ማሕበሩ እየተጠናከረ በሚመራበት ላይ እያተኮረ ሲመራ ቆይቶ ጸሐፊ አቶ ጃርሶ ገንዘብ ያዥ ዶር/ ክንፈ በመመረጥ በቀረበው ያንኑ ዕለት መዋጮ የመጀመር ሃሳብ ላይ ተስማምተን የመጀመሪያው መዋጮ፣ 34. ብር ከስንትስ ሳንቲም ተሰበሰበ። የመጀመሪያው ቤተክርስቲያናችንን የተመለከተ ስብሰባና የመነሻ ካፒታላችን ይህንን የመሰለ ነበር።

የፋሲካ በዓልን በቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን

የፋሲካ በዓል እየተቃረበ ነበር። በቅርብ አብረን እንኖር የነበርን እነ ዶ/ር ሙሉመቤት ኃይለሥላሴ፤ ወ/ሮ ወሰን ጉግሣ ዶር/ ዓለማየሁ በቀለ ጋር በየበአላቱ የመገናኘት ዕድል የነበረንም ቢሆን በቤተክርስቲያን ከሌሎች ወገኖቻችንም ጋር የመገናኘቱን እድል የከፈተልን የፋሲካ በዓል ነበር። እንግዴህ ቤተክርስቲያንም ካሕንም ያለን መሆናችንን ስላወቅን ሰፋ አድርገን ስለምናደርገው የፋሲካ በዓል ዝግጅት መነጋገርና ኃላፊነትም መከፋፈል እንደሚያስፈልገን ተረዳን። ለበዐል የሚሆን እህል ውሃ እንዲሁም የመመገቢያ ዕቃዎችን የሚያመጡ ተደለደሉ። ሁሉም የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ተሰማሩ። በቀዳም ሥዑር ምሽት ሁሉም እየተጠራራ ቤተ ክርስቲያናችን ሒንሲዴል ወደነበረው የግብጻውያን ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን አመራን።

ከቤተክርስቲያኗ ግቢ እየመጣ የሚቆመው መኪና ሁሉ ባማረ ያሸበረቀ የሐገር ልብስ የተዋቡትን ሕጻናት ልጆችና አዋቂዎችን እያመጣ ያፈስ ጀመር። ወዲያው ወደቤተክርስቲያኗ መግቢያ ስናመራ ከዚያ መጀመሪያ ከማስታውሳቸው እስካሁን ባገልግሎታቸው ከቤተክርስቲያናችንም ካልተለዩት ውስጥ ተስፋሚካኤል ካሣዬና ሃብተሚካኤል ካሣዬ በትሁት ምግባር እየተቀበሉ ቦታ ቦታ አስያዙን። ፈጣሪውን ለማመስገን ለማወደስና ለመማጸን ምእመናኑ የተሟላ ድርጅትን መጠበቅ የማያስፈልገው መሆኑን የሚያምኑትና “አንድ አይጤስ አንድ አይቀድስ” የሚባለው አነጋገር ጊዜንና ሥፍራን ለይቶ መሆን አለበት በማለት ያኔም ከዚያም በኋላ ለብዙ ዓመታት በሥራ ያስመሰከሩ አባታችን በደስታ ሁላችንንም ተቀብለው በመግቢያ ጸሎት ተዘጋጅተው ሊረዱ የመጡትን ዲያቆናት፣ ዘውዴ ለማንና አምሃ ተሰማን ይዘው በቺካጎ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥነስርአት የመጀመሪያውን የትንሣኤ በዓል በቅዳሴ እንድናከብር አደረጉ።

እንዲህ በሚያስደስትና የረካ መንፈስ ጸጥታም በሞላበት ቅዳሴውን ፈጽመን ካባታችን ቡራኬ ከተቀበልን በኋላ ወደ ግብሩ አዳራሽ ወርደን በጸሎትና በምስጋና የቀረበውን የፋሲካ ማዕድ ተሳትፈን ያልተዋወቅነው እየተዋወቅን በየበዓላቱም እንዲሁ ለመገናኘት በተሞላ ተስፋ ተሰነባበትን። ይህ በሃይማኖትና በማሕበራዊ ኑሮ የመደጋገፍ አጀማመር እየተጠናከረ ሲሔድ በቺካጎም የኢትዮጵያውያን ነዋሪዎች ቁጥር እየበረከተ ሲመጣ በዓላትን የምናከብርበት ብቻ ሳይሆን ዘወትር ሰንበትንም ልናከብርበት የሚቻልበት ከቺካጎ ብዙ ርቀት የሌለው ልንጠቀምበት የምንችል ቤተክርስቲያን መፈለግ ተጀመረ።

በተለይም አባታችንና ነፍሱን ይማራትና ዶ/ር አብርሃም ደሞዝ ፣ ለኖርዝዌስተርን ዩኒቨርሲቲ እና በአካባቢው ለነበሩ የሃይማኖት መሪዎች ቅርበትና እውቅና ስለነበራቸው በኤቫንስተን የዩናይትድ ሜቶዲስት ቤተክርስቲያንን መሪዎች በማነጋገር ሕንዳውያን ክርስቲያኖች ይጠቀሙበት የነበርውን፤ እነሱ እንደሚለቁና፤ እንደለቀቁም እሑድ እሑድ ለመብራትና ለጽዳት የእርዳታ ክፍያ በመክፈል ልንጠቀምበት እንደምንችል ሊያደርጉ ቻሉ። (ዶር አብርሃም ደሞዝና ባለቤታቸው ወይዘሮ አስቴር ከሌሎቻችን በህይወት ካለን ከሌሉም ወንድም እህት ልጆችና የበረከት ተካፋዮች ጋር በሃይማኖትና በህብረሰብነት ተጠናክሮ መቋቋም ካባታችን ጎን ያልተለዩ ነበሩ፡፡ በመቀጠልም በኖርዝዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ጋሬት ሴሚናሪ እሑድ እሑድ ጧት በመሰብሰቢያው አዳራሽ ልንገለገል የምንችል መሆናችን ተገልጾልን አባታችን ለሦስት ወራት ኪዳን ጸሎትና ትምሕርት ሲሰጡን ቆየን። ይህንን ለማደራጀትና ለፍቃዱም መሪዎች የነበሩትን ዶ/ር ፔሪንና ዶ/ር ሎዎንዴልን ቤተክርስቲያናችን ከልብ ታመሰግናለች (ሁለቱም በሥጋ ሞት ተለይተውናል)። ይህ ሲሆን ሌላው እራሳችንን መጀመሪያ በቦርድ ቀጥሎም በላዕካን አርድእት አገልግሎት ሥራን ለመምራት በሚቻልበት ስልት ቅደም ተከተል በመስጠት እንዲቀነባበር ተደረገ።

በኤቫንስተን በዩናይትድ ሜቶዲስት ቤተክርስቲያን በመጠቀም ያሳለፍነው 15 ዓመት

በኤቫንስተን የዩናይትድ ሜቶዲስት ቤተክርስቲያን የጀመርነው የተቀነባበረ አመራር ጥሩ መስመር እንዲይዝ ምእመናኑም መንፈሳዊ አገልግሎቶችን አግኝቶ ቤተክርስቲያኗንም በሚደግፍበት ልዩ ልዩ አቅጣጫ እንዲጠናከር እጅግ ጠቃሚ ልምድን ሰጥቶናል። ከሁላችንም የበለጠ አባታችን የየዘርፉን በተለይም በእምነትና በተግባር ኅብረተሰቡ ተጠናክሮ ልዩ ልዩ አገልግሎትን በሚያገኝበት በሚሰጠውም መንፈሳዊ ትምሕርት የኑሮና ያስተሳሰብ ለውጥን በሚያደርግበት የደከሙት የሚፈራረቀውንም የቺካጎ የክረምት ቁርና የበጋ ሃሩር ተቋቁመው ለተጠሩበት መንፈሳዊ ተልዕኮ እጅግ አጥጋቢ መልስ ለመስጠት ያላቋረጠ ጥረት አድርገው ያሸነፉበት በኤቫንስተን በቆየንበት ዓመታት ነው። ለዚህም አስተሳሰብ ድጋፍ ቢያስፈልግ የሚሰጠው ሃይማኖት ላይ ያተኮረ ሕብረሰባዊ አገልግሎት መሠረቱን ሳይለቅ የባእድ አገር የኑሮ ግዳጅንና ሕብረሰቡ ኑሮውን ለመመሥረት የሚኖርበትን ጫና ከግንዛቤ በመውሰድ ታቦት ይዘው እየተንከራተቱ ለራሳቸውም ደሞዝ ይከፈለኝ እረፍት ያስፈልገኛል ሳይሉ በተፈቀደልንም ቤተክርስቲያን በየሳምንቱ በመጋረጃ የሚሠራ መቅደስ እያዘጋጁ ያሳለፉዋቸው 15 ዓመታት አይረሱም።

በኤቫንስተን በቆየንባቸው ዓመታት በዩናይትድ ሜቶዲስት ቤተክርስቲያን ለመጠቀም መውጣትና መግባታችን እንደነዋሪዎቹም የነዋሪነት ስሜት ፈጠረልን። ይህን ብለውም እንደሆን እንጃ ዓመታዊው የባሕር ዳር ባሕላዊ ዝግጅት በተቃረበበት ጊዜ እኛም የኢትዮጵያዊነታችንን ባሕል በሚያሳዩ ዝግጅቶች እንድንሳተፍ ተጋበዝን። ትንሽ የመግቢያ ክፍያም ቢኖረው ገቢም ሊገኝበት ይችላል በሚል ሌላው ቢቀር የባሕል ምግባችንን ለማስተዋወቅና በሽያጭም ለምናደርገው የቤተክርስቲያን ሕንጻ ግዢ ገቢ እናገኛለን ብለን ተመዘገብን። ነፍሷን ይማርና ወይዘሮ አስቴር ገብረማርያምና ቤተሰቦቻቸው የሚኖሩት በኤቫንስተን ስለነበር በዝግጅቱ ተካፋይ እንድንሆን ምዝገባውን የምታቀነባብረው እርሷ ነበረች። እንደተለመደው ልዩ ልዩ ያገር ምግብ ከየቤቱ ተሰናድቶ ይመጣና እዚያው ከተተከለ ድንኳን ውስጥ ተገዝቶ የቀረበ ሥጋ በመልካም አዋዜ እየታሸ ተጠብሶ በእንጀራ ከሌላው ከቤት ተሠርቶ ከመጣው ምግብ ጋር በሰሐን በሰሐን እየሆነ ይሸጣል። ተሳትፎውና የባሕል ዝግጅቱ አካል መሆኑ ምግባችንንም ማስተዋወቁ እየተዘዋወርንም የሌሎችንም ምግብ መቀማመሱ ሱቪኔርም ማየቱና መግዛቱ በያመቱ በበዓሉ እንድንሳተፍ ቢገፋፋንም የገቢ ማግኘቱ ላይ አልተሳካልንም። ወደኋላ መለስ ብለን ስናሰላው አንዱ ምክንያት ይሆናል ብለን የገመትነው ይዘነው የመጣነው ቸር ባሕል፤ ሲሆን በግብዣ አልያም ተረፍረፍ አርጎ በመስጠት ላይ የተመሠረተው ሳይሆን አይቀርም ብለን አሰብን። ይሁንና ተሳትፎው ለአንድ ዓላማ በሕብረት የመሰለፍንና እራስን የማደረጃጀትን ቀደም ብለን የጀመርነውን ሂደት በማጠናከር ተጨማሪ ትምሕርት ሆኖናል።

የራሳችን የሆነ የቤተክርስቲያን ሕንጻ ሊኖረን የሚችልበትን መንገድ ማውጠንጠን ቀጠልን። በኤቫንስተን በቆየንበት ዓመታት ምንም እንኳን የሃይማኖት አገልግሎቱና በቤተክርስቲያን ቤተሰብነት መደራጀቱ ያለብዙ ችግር ቢቀጥልም የሰዓታትና ሌላ ገደብ ሳይኖርብን የመጠቀሙ ፍላጎታችን እየጎላ ሔደ። ለዚህ አስተሳስብ መልካም አማካሪዎችና ረዳቶች እንዲሆኑን የተለያዩ የቤተክርስቲያናት መሪዎችን በአማካሪነትና በቤተክርስቲያን ሕንጻ ፍለጋ ረዳትነት እልፍ ሲልም ለሁል ጊዜ የመገልገያ ሕንጻ ችሮታ እንዲረዱን በዶ/ር ፔሪና ዶ/ር ለዎንዴል ደጋፊነት ልንጠይቃቸው ጋበዝን። ካማካሪዎቹ ጋር የመጀመሪያው ስብሰባችን እዚያው ቤተክርስቲያን ግቢ አነስተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ እንዲሆን ተስማምተን ከየቤቱ ጣፍጦ ተሰናድቶ ከመጣ የሐገር ባሕል ግብዣ በኋላ ምክክሩ ተጀመረ። ስድስት ያህል የቤተክርስቲያን መሪ ተጠሪዎች ከኛ ከጋባዦች ጋር ወደ 16 ያህል ነበርን።

ስለአቋማችንና ስለእቅዳችን ለውይይቱ መግቢያ ካቀረብነው ውስጥ በዚያን ጊዜ በገንዘብ ያዥነት የሚያገለግለን ወንድማችን አቶ መስፍን ተፈራ ቤተክርስቲያን ለመግዛት እስካሁን አቅማችን የቱን ያህል እንደሆነና ምን ያህል ትግልም እንድሚያስፈልገን ግልጥ አድርጎ አቀረበ። ሌሎቻችንም እንዲሁ የኅብረተሰቡን ኑሮ ጀማሪነትና ውሱን አቅም በማስረዳት ውይይቱ ክፍት ሆነ። የምክክሩ ውጤት የሚያረካና ልንጠቀምባቸው የቻልናቸውን ውጤቶች የያዘ ነበር። ከሁሉም ትዝ የሚለኝ የሕብረሰባችንን የገቢ ማነስና አለመደራጀት ደጋግመው በመስማታቸው ነው ብዬ አምናለሁ ዶ/ር ለዎንዴል አንድ የምሰጣችሁ ምክር አለ ብለው ጀመሩ “ ሰው አቅም የለውም፤ ገቢ የለውም በማለት ባለው ሊቸር፤ የመቻልን ጸጋና በተሳትፎም የመንፈስ መርካት የማግኘትን ውጤት ከመንፈግ መጠንቀቅ ያስፈልጋል” በሚል ዘጉ። ይህ ስብሰባ በርግጥ ሕንጻ ቤተክርስቲያን እንዲኖረን በምናቅደው እቅድ ግፊት ከሰጡንና የየግላችን ጥረት ሊደርስ ከሚችልበት አልደረሰም ብለን እንድናምን ካደረጉን አንዱ ነበር።

የመጨረሻው ምእራፍ መጀመሪያ

ጊዜ ሁሉን ይፈታል የሚለው አባባል ትኩረቱ የቀናት የወራትና የዓመታት ማለፍ ላይ ብቻ እንዳይሆን መገንዘብ ተገቢ ነው። ጊዜ ይበልጡኑ ለአስተሳሰብ ለውጥ፤ ለዕቅድና ለአቅጣጫ መሻሻል፤ ለበለጠ ያሠራር ዕውቀት፤ ከጥፋት የመማርም ዕድል ይፈጥራል። እኛም ጊዜ ይህን ያተረፈልን መሆኑን የተሻለ የገንዘብ ማግኛ ዘዴ በሥራ ላይ እንዲውል ማድረጋችን መስክሯል። ከእለታት አንድ ቀን ቦርዱ የተሰበሰበበት ዋናው መነጋገሪያ የቤተክርስቲያን ሕንጻ መግዛትና ለዚህ ቀዳሚ የባንክ ተከፋይ ማግኘት ላይ ሆነ። ይህንን በሥራ የሚተረጉም ኮሚቴ ለማቋቋምና ኮሚቴው የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴ ፈጥሮ እንዲያቀርብ ቦርዱ ወስኖ ኮሚቴው ተሰየመ። ከቦርዱ በተጻፈ ደብዳቤም እያንዳንዱ አባል አገልግሎት እንዲሰጥ ተጠየቀ።

በተሰየመው ኮሚቴ እንዲያገለግሉ የተጠየቁት፤ አቶ ዘውዴ በዳዳ፤ አቶ ሳሙኤል በቀለ፤ አቶ ተስፋሚካኤል ካሣዬ፤ አቶ ደሳለኝ ካሣ፤ ዲያቆን እስጢፋኖስ ስዩም፤ ወይዘሪት ኑኑ ጌታቸው (ነፍሷን ይማር በሥጋ ሞት ተለይታናለች)፤ ወይዘሪት ራሔል ክንፈ፡ ሲሆኑ ዲያቆን እስጢፋኖስና ወይዘሪት ራሔል በመፈራረቅ በሊቀመንበርነትና በጸሐፊነት አገልግለዋል። አቶ ሀብተ ሚካኤል ካሣዬ ቦርዱን ወክሎ በታዛቢነትና ገለጻ ለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ለመርዳት ተሳታፊ ነበር። ኮሚቴው ከመጀመሪያው ቦርዱ ባተኮረበት የገቢ ማግኛ ዝግጅት ላይ በሚያረካ ሁኔታ እየተገናኘ ተነጋግሮና እቅዶች አውጥቶ ትልቅ የራት፤ የቅርሳቅርስ መጎብኛና የትምሕርታዊ ንግግር መስሚያ ዝግጅቶች ተቀነባበሩ። ቀደም ብለን ባማካሪነት የረዱን የቤተክርስቲያናት መሪዎችና ሌሎችም የዩኒቨርሲቲ መምሕራን ተጋበዙ። ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሴሜቲክ ሃይማኖትና ባሕል ፕሮፌሰር የምሽቱ ተናጋሪ እንዲሆኑም በቦርዱ ተጋበዙ። በዚህ ምሽት በቤተክርስቲያናችን ታሪክ እጅግ የተሳካና ላቀድነውም ከሌላውም ጊዜ ሁሉ የበለጠ ባንድ ምሽት $ 65,000 ተሰብስቦ ሌላ 65,000 ብር በየጊዜው ሊከፈል ተስፋ የተገባበት ነበር።

ከሌላ ስቴቶች በተለይ ከሚኔሶታ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ሊረዱን የመጡትን መዘምራንና በተለይ ከመዘምራኑ መካከል ሰብለ በዝማሬና በከበሮ እየተዟዟረች የየሰዉን መንፈስ እጅግ በመቀስቀስ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጋ ነበረ። በፕሮፌሰር ኤፍሬም የተሰጠውን ትምሕርታዊ ገለጻ ብዙዎች፤ በተለይ እንግዶቻችን እንዳደነቁትና በጠቅላላውም በምሽቱ ዝግጅት የተደሰቱ መሆናቸውን ባድናቆት አካፍለውናል። ለኛም ይህ ገቢ ነበር የምንገዛውን የቤተክርስቲያን ሕንጻ ማየት ያስጀመረንና እስከፍጻሜውም እንድንገፋ ያበረታታን። ይህ የሆነው በምዕራብያውያን አቆጣጠር ሰኔ 6 ቀን 1996 ነበር። ይህን ለማቀነባበር የተሰየመው የኮሚቴ አባሎች፤ ኋላ እራሳቸውን የጁን ሲክስ (June six) ኮሚቴ ብለው ራሳቸውን ይጠሩበት ነበር። ቤተክርስቲያናቸው፤ የሰየማቸውም ቦርዱ እጅግ አመስግኗቸዋል። ዲያቆን እስጢፋኖስ ስዩም፤ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ገዝተን እስከወጣንበት ሁለት ዓመት ጊዜ በተስፋ የተያዘውን በማሳሰብና በማስታወስ የሚበዛው እንዲገባ በማድረግ ተጨማሪ አገልግሎቱን አበርክቷል።

በዕለቱ የራት ግብዣ የተሰበሰበው ገቢ ቀደም ብሎ ከባንክ ከነበረን ጋር ለተቀዳሚ ክፍያ ይበቃል በማለት፤ ለሽያጭ የወጡ ሕንጻ ቤተክርስቲያናትን በጋዜጣም በጥቆማም በቡድን እየሆንን ማፈላለግ ጀመርን። ብዙዎቹ ወደኅብረተሰቡ መኖሪያ ቀረብ ብለው የተገኙት ፍላጎታችንን የማያሟሉ ከመሆናቸውም በላይ ዋጋቸው የማይቀመስ ነበር። ጥቂት የማይባሉ ቤተክርስቲያኖችን ከተመለከትን በኋላ ቀድሞ የሰርቢያ ቤተክርስቲያን የነበረ 9805 ደቡብ ኮሜርሻል አቬኑ ላይ ያለ አካባቢው ጭምር በልማት ድርጅት ተገዝቶ ቤተክርስቲያኑ ለሽያጭ ወጥቶአል ማለትን እንደሰማን ብዙዎቻችን፤ በተለይም አባታችን አባ ተክለሚካኤልና ወንድማችን አቶ ካሣሁን አየለ ደጋግመን  ስናየው ቆየንና ያለንን አስተሳሰብ ተካፈልን። እጅግ የሚበዙት የቤተክርስቲያኑ ቤተሰቦች ቤተክርስቲያኑን መውደዳቸውን ገልጸው እንዲገዛ ደገፉ። ጥቂቶች ከመኖሪያ ሰፈር ይርቃል በማለት ቅሬታቸውን አስታወቁ፤ ጥቂቶችም የአካባቢውን ጸጥታ በመጠራጠር ድጋፋቸውን ነሱ።

ጸጥታውን በሚመለከት ጥቂቶቻችን ከሐሮልድ ዋሺንግተን መጻሕፍት ቤት ሔደን ሰፊ የየመንደሩ የወንጀል ጥናት መዛግብትን በመመርመር ቤተክርስቲያኑ ያለበት ሰፈር ወንጀልን በሚመለከት ብዙዎች ኢትዮጵያውያን ከሚኖሩበት ከሰሜኑ የቺካጎ አካባቢ የተሻለ መሆኑን ተረዳን። ቤተክርስቲያኑን ለመግዛትም 95 በመቶ የሚሆነው የቤተክርስቲያናችን ቤተሰብ እንዲገዛ በማጽደቁ ቦርዱ በመግዛቱ ቆርጦ የባንክ ብድር መፈለግ ጀመረ። የሐሪስ ባንክ የተሻለ የወለድ ልክ በመስጠቱ ተዋውለን በምዕራባውያን አቆጣጠር በመጋቢት ወር 1998 ዓም የቤተክርስቲያኑን ሕንጻ ከመንገድ ባሻገር ካለ ሰፊ የመኪና ማቆሚያ ጋር ገዛን። የቤተክርስቲያኑ ሕንጻ በ1926 ዓም በሰርቢያኖቹ በእጃቸው እንደተሠራ በየጊዜው ከቤተክርስቲያናችን የማይጠፋ ወዳጃችንና ደጋፊ የሆኑ የሰርቢያ ተወላጅ ቀድሞም ለብዙ ዓመታት በዚሁ ቤተክርስቲያን ቤተሰባቸው ይገለገል የነበረ ወ/ሮ ሚራ ሳቪች በየጊዜው ከታሪኩ ጋር ያጫውቱናል። በዚያ ዘመን ከምሥራቅ አውሮፓ በልዩ ልዩ ሙያ የሰለጠኑ ሰርቢያውያን በብዛት ወደአሜሪካ መጥተው በአካባቢው የብረት ማውጫ ትልቅ ኩባንያ በነበረበት steel city ተብሎ ይጠራ በነበረው ለሥራው ሲሉ ሰፍረው ቤተክርስቲያናቸውንም ሊያቋቁሙ ቻሉ። በአሁኑ ጊዜ ወደ አስር ማይል ዝቅ ብሎ ላንሲንግ ከተባለ መንደር ሰፊ ቦታ ገዝተው ቤተክርስቲያናቸውንና ሰፊ የሚያከራዩት የሕዝብ መገልገያ አዳራሽ ከዚያ በማቋቋማቸው ነው ይሄኛውን የሸጡት።

የግዢ ቅደም ተከተሉን ለማሟላት ከሐሪስ ባንክና ከሕንጻው ባለንብረት ኩባንያ ወኪሎች ጋር መደራደሩና መፈራረሙ ተከናውኖ ሕንጻውም የተሠራው በድሮ አስቤስቶስና ሌድ ለጤና ጠንቅ መሆናቸው የጎላ እውቅና ባልነበረት ዘመን ስለነበረ በምርመራ ለጉዳት ሊያጋልጡ ይችላሉ የሚባሉት እነዚህ የግንባታ ግብዓቶች በተለይ ከማሞቂያ ሞተር ክፍልና ከወለሎች እንዲነሡ ተደረገ። ከዚያም ሕንጻውን በመረከብ የራሳችን የሆነ ቤተክርስቲያን ባለንብረቶች ሆንን። ቤተክርስቲያን ስንፈልግ በቆየንበት ጊዜ ሁሉ ከልባችን የገባ ወይም በምንገዛው አቅም አካባቢ የሆነ ለሁለት ዓመታት ሳያጋጥመን በመቅረቱ ብዙ ጊዜ ብዙዎቻችን የምንለው “መድኃኔዓለም ለኛ ያለውን ያቆየናል” ነበር። ይህም ከብዙ የቤተክርስቲያናችን አባላት አፍ ተሰምቷል። የሕንፃ ቤተክርስቲያኑ አቀማመጥ፤ የምንጠቀምባቸው ዕቃዎች ተሟልቶ መገኘት፤ ብቃት ያለው የሰንበት ትምሕርት ቤት ከቅጥሩ ግቢ መኖር፤ እንደልብ የመኪና ማቆሚያ መኖሩ በዚያ ላይ ዋጋው የምንወደው መሆኑ እውነትም መድኃኔዓለም ያቆየልን ነው። ለጥቂት ወራት ለመቅደሱ ሥራና ለአገልግሎት የሚሆኑ አባታችን በዝርዝር ያስቀመጧቸው በምእመናኑ እየተገዙ ወይም እየታዘዙ እስኪሟሉና የመቀባትና የማጽዳት የትብብር ሥራ እስኪፈጸም፤ አባታችንም ለመቅደሱ ውስጥ አገልግሎት አስፈላጊ የሆኑትን ከኢየሩሳሌም ይዘው እስከሚመጡ አገልግሎቱ የተሟላ ሳይሆን ቆየ። የቤተክርስትያኗንን የሰንበት ትምሕርት ቤቱንና የካሕን መኖሪያውን ውስጡንና ውጪውን ለማጽዳትና ለመቀባት ጥቂት ሳምንታት አስፈልጎ ነበር። ሁሉም የቤተክርስቲያኗ ቤተሰቦች ሴት ወንድ ልጅ አዋቂ አዛውንት ሳይል ከልብ በሥራው ተሳትፈው ሕንጻዎቹን የበለጠ እንዲጸዱ አድርገዋል፤ የመድኃኔዓለም ቸርነት ምንጊዜም አይለያቸው።

በቤተ መቅደሱ ላይ ተሥለው ያሉትን ቅዱሳት ሥዕላት የቤተክርስቲያኗ ቤተሰቦች ገንዘብ በማዋጣት በሠዓሊ እንዲሳል አድርገዋል። ለሥዕሎቹ ወጪ አስተዋጽኦ ያደረጉትን ሁሉ በተጨማሪ በማቀነባበሩም ያገለገሉትን ዶ/ር ዓለማየሁ በቀለን ወሮ ወሰን ጉግሳን አቶ ኤፍሬም ክፍሌን ቤተክርስቲያናችን በጸሎቷ ታስታውሳቸዋለች። ይህ ሁሉ በቅደም ተከተል ተስተካክሎ በኋላ በእኛ አቆጣጠር መጋቢት 27 ቀን 1992 ዓም (በምዕራባውያን በ1999) ታቦቱ ለእለቱ ካረፈበት የድንኳን ማረፊያ በተጋበዙ ብዙ ካህናት፤ ዲያቆናትና የቤተክርስቲያናችን ቤተሰቦች፤ የቺካጎና ያካባቢ ስቴቶች የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታዮችም በተገኙበት ታጅቦ ከቤተክርስትያኗ በዝማሬ በእልልታና በጭብጨባ ገባ። ስለዚህ በቺካጎ ከተማ፤ 9805 ደቡብ ኮሜርሻል ላይ የነበረው ቅዱስ ሚካኤል የሰርቢያኖች ቤተክርስቲያን፤ ደብረጽዮን መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ተብሎ በክቡር አባታችን ተሰየመ ። አገልግሎቱም እየተጠናከረ አባታችን ሊቀሊቃውንት አባ ተክለሚካኤል በመሠረቱትና ቤተክርስቲያኗን ተባብሮና ተደጋግፎ በመምራት የተዉልንን ፋና በመከተል ቀጥሎአል። ወደፊትም ቤተክርስቲያኗ ስትቋቋም ጀምሮ የነበራትን በር ምቱ ይከፈትላችኋል እሹም ታገኛላችሁ ባለው የወንጌል ቃል መሠረት ምእመናኖችዋ ከቸሩ መድሓኔዓለም ጋር በመገናኘትና መንፈሳዊ ህይወታቸውን በማዳበር ለልጅልጅ የሚያስተላልፏት እንድትሆን የተቀደሰ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

Scroll to Top
Scroll to Top