እንኳን ደህና መጡ!

ደብረ ጽዮን መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፤ ቺካጎ!

ማስታወቂያ!

ኪዳን እና ቅዳሴ የሚደርስባቸው ወርሃዊ እና ዓመታዊ በዓላት

ወር በገባ በ 3 የእመቤታችን በዓታ ውስተመቅደስ – ኪዳን /ዓመታዊ በዓል ቅዳሴ
ወር በገባ በ 12 የመል አኩ ቅዱስ ሚካኤል – ኪዳን
ወር በገባ በ 19 የመላኩ ቅዱስ ገብር ኤል – ኪዳን
ወር በገባ በ 21 የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም – ኪዳን
ወር በገባ በ 24 የአባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖት – ኪዳን / ዓመታዊ በዓል ቅዳሴ
ወር በገባ በ 27 የጌታችን የመድሐኒዓለም በየወሩ ቅዳሴ

እምነት
የቤተክርስቲያናችን እምነት መሰረት

ቤተክርስቲያናችን መጻሕፍተ ብሉያትንና ሐዲሳትን እንዲሁም በመንፈሳውያን አባቶችና ሊቃውንት የተጻፉትን አዋልድ መጻሕፍት ትቀበላለች። ቤተከርስቲያናችን በቤተክርስቲያን አባቶች ዘንድ ጸንቶ በቆየው አሰትምህሮ የእግዚአብሔርን የባሕርይ አንድነትና የአካል ሦስትነት ታምናለች።

ቤተክርስቲያናችን ሰውን ለማዳን በአባቱ፤ በራሱና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ እግዚአብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ የነሳውን ሥጋችንን በፍጹምነት መዋሐዱን ከተዋሐደ በኋላ መለኮትና ሥጋ አንድ አካል አንድ ባሕርይ መሆኑን፤ በመስቀል ላይ መሰቀሉን፤ መሞቱን፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ መነሳቱን፤ በአርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ማረጉን ፤ በክብር በአብ ቀኝ መቀመጡን፤ ዳግመኛ በጌትነት የሚመጣ መሆኑንና ለእኛም ተስፋ ትንሳኤንና ዘለዓለማዊ ሕይወት መስጠቱን ታምናለች።

ቤተክርስቲያናችን ከአብ የሠረጸው መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ጋር በመለኮት ዕሩይ (እኩል) መሆኑን ታምናለች።

ቤተክርስቲያናችን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ዘለዓለማዊ ድንግልና፤ የአምላክ እናት መሆንዋንና በጸሎትዋም እንደምታማልደን ታምናለች፤ እንዲሁም በቅዱሳን መላእክት፤ ሐዋርያት፤ ሰማእታትና ጻድቃን ጸሎትና ምልጃ ታምናለች።

ቤተክርስቲያናችን ሦስት መቶ አስራ ስምንቱ ሊቃውንት አባቶቻችን በኒቂያ ተሰብስበው የወሰኑትን ጸሎተ ሃይማኖት የእምነቷ መሠረት አድርጋ ትቀበላለች።

ቤተክርስቲያናችን በኒቂያ፤ በቁስጥንጥንያና በአፌሶን ጉባኤዎች የተሰጡትን የሃይማኖት ድንጋጌዎችን ተቀብላ ትከተላለች።

ዓላማና ተልእኮ

የደብረጽዮን መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከቀረጥ ነጻና ትርፍ አልባ የሃይማኖታዊ ተቋም እንደመሆኗ መጠን የተመሠረተችበት ዋና ዓላማ ለምእመናን ሃይማኖታዊ አገልግሎት ለማበርከት ነው። ይሕንን ዓላማ ተቀዳሚ በማድረግ ከዚህ በመቀጠል የተዘረዘሩትን ተልዕኮዎች ተግባራዊ ታደርጋለች፤

ሀ.   የደብረጽዮን መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናኗን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተክርስቲያን      እምነትንና ሥርዓተ አምልኮን በመከተል እንዲገለገሉና እንዲያገለግሉ ታደርጋለች።

ለ. ቤተክርስቲያኗ መንፈሳዊ አገልግሎቷን ለማጠናከርና የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌለ መንግሥት በሰፊው ለማዳረስ፤ እንዲሁም አገልግሎቷን አጠናክራና አስፋፍታ የእምነታችን መሠረት ሳይለወጥና ሳይበረዝ ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ ሳታቋርጥ ትሠራለች።

ሐ. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት እምነት መሠረት ለምእመናን የጥምቀት፣ የጋብቻ እና የፍሐት አገልግሎት ትሰጣለች።

መ. አዳጊ የ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት እምነት ተከታይ ወጣቶችን ሃይማኖታቸውን፤ ኢትዮጵያዊ ቋንቋቸውንና ባሕላቸውን በማስተማር የቤተ ክርስቲያኗ ተረካቢ ዜጋ እንዲሆኑ ታዘጋጃለች።

ሠ. በኢትዮጵያ የሚገኙ ገዳማትንና አድባራትን ትረዳለች።

ረ. በየእስር ቤቱ በተለያየ ምክንያት የታሰሩትን፤ በየሆስፒታሉ በሕመም የሚሰቃዩትን፤ ጠዋሪ ቀባሪ የሌላቸውን የደከሙ አዛውንቶችንና ችግረኞችን በተቻለ መጠን በመርዳትና፡ በማጽናናትና የአለኝታነት ድጋፍ ትሰጣለች። 

ሰ. ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ጋር በሰብአዊ እርዳታ ጉዳዮች ላይ በመተባበር ለማንኛውም ሕብረተሰብ እርዳታ በሚደረግበት ጊዜ በእርዳታ አሰጣጡና በሥራው ትካፈላለች፡ ትሳተፋለችም።

Scroll to Top